ለታካሚዎች መረጃ

የሄሞዳያሊስስን ተደራሽነት መረዳት

በእነዚህ ገፆች ውስጥ፣ የሄሞዳያሊስስን ተደራሽነት አስፈላጊ ዝርዝሮችን እንገልፃለን – ምን እንደሆነ፣ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ እና እንዴት በህይወትዎ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል። ታካሚም ሆኑ ተንከባካቢ፣ እዚህ አስተማማኝ እና የተመቻቸ የሄሞዳያሊስስ ተደራሽነት ለማግኘት በጣም ጠቃሚ የሆነ ጥሩ ግንዛቤ እና እውቀት ያገኛሉ።

የዲያሊሲስ አገልግሎት ምንድን ነው?

ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ የሚከሰተው አንድ ህመም ኩላሊትዎን ሲጎዳ ነው። በብዙ አጋጣሚዎች ጉዳቱ የሚከሰተው እንደ ከፍተኛ የደም ግፊት ወይም የስኳር በሽታ ባሉ ሥር የሰደዱ ሁኔታዎች ምክንያት ነው።

ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ከተፈጠረ በኋላ ጉዳቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ ይሄዳል። ከጊዜ በኋላ ኩላሊቶችዎ መደበኛ ስራቸውን ያቆማሉ፣ እና ቆሻሻዎች እና ፈሳሾች በሰውነትዎ ውስጥ ይከማቻሉ።

ኩላሊቶችዎ ከ85-90% ስራቸውን ሲያጡ የኩላሊት ሽንፈት ወይም የመጨረሻ ደረጃ የኩላሊት በሽታ ውስጥ ይገባሉ። ቆሻሻን እና ከመጠን በላይ ፈሳሾችን በራሳቸው ማጣራት አይችሉም። በዚህ ደረጃ ጤናማ ለመሆን የዲያሊሲስ አገልግሎት ያስፈልግዎታል።

በመጨረሻው ደረጃ ላይ ያሉ የኩላሊት ህመም ያለባቸው ሰዎች ኩላሊታቸው በበቂ ሁኔታ ስለማይሰራ ጤነኛ እንዲሆኑ እና በሕይወት ለመቆየት እንዲችሉ የኩላሊት ተግባራቸውን ለመተካት በዲያሊሲስ ላይ ጥገኛ ናቸው።  ሄሞዳያሊስስ ኩላሊቶች በማይሠራበት ጊዜ ቆሻሻዎችን እና ተጨማሪ ፈሳሾችን ከደምዎ ውስጥ የሚያስወግድ ህክምና ነው።

ዳያሊስስ እንዴት ይሰጣል?

ሄሞዳያሊስስን ከመደረጉ በፊት ደሙን ከታካሚ ሰውነት ውስጥ ለማውጣት፣ ከቆሻሻ ምርቶች እና ተጨማሪ ፈሳሾች ለማጽዳት እና ከዚያም ወደ ሰውነታችን የሚመለስበትን መንገድ/መዳረሻ ማግኘት ያስፈልጋል።  ደሙ በነዚህ መንገድ በኩል ወደ ዲያላይዘር ወይም ሰው ሰራሽ ኩላሊት የሚወጣበት እና ወደ ሰውነትዎ የሚመለስበት መንገድ ነው።

የደም ስር ቀዶ ጥገና ሐኪም ዘላቂ የሆነ የዳያሊስስን መዳረሻ አገልግሎት የመፍጠር ልምድ አላቸው፣ ይህም ሕክምናውን ቀላል ያደርግልዎታል። ለሄሞዳያሊስስ በጣም ጥሩው የመዳረሻ አይነት ከቆዳው በታች አብዛኛውን ጊዜ በክንድ የታችኛው ክፍል ውስጥ የደም ወሳጅ ስርን ከደም መላሽ ስር ጋር በማገናኘት የዳያሊስስን ተደራሽነት በመፍጠር ነው። ይህ ግንኙነት ደም ወሳጅ ስር መጠኑ እንዲጨምር እና እንዲወፈር ያደርገዋል ስለዚህ መርፌዎችን ለማስገባት ቀላል የሆነ ቦታን ይፈጥራል።

ምን ማድረግ አለቦት?

  • የዳያሊስስን ሕክምና ከመጀመርዎ በፊት ሐኪምዎ ቢያንስ ከስድስት ወራት በፊት የሄሞዳያሊስስን ተደራሽነት በመፍጠር ልምድ ወዳለው ልዩ የደም ስር ቀዶ ጥገና ሐኪም መላክ አለበት።
  • አንዴ ዶክተርዎ ዳያሊስስ እንደሚያስፈልግዎ ከነገረዎት ቀዶ ጥገናው የሚካሄድበትን ክንድ መጠበቅ አለቦት። የሆስፒታል/የህክምና ሰራተኞች በዚህ ክንድ ላይ ደም እንዲወስድ ወይም መርፌ መወጋት እንዲሁም የደም ግፊትዎን ከዚህ ክንድ ለመውሰድ እንዲጠቀም በፍጹም አይፍቀዱ።

ለሄሞዳያሊስስ የተለያዩ የመዳረሻ አማራጮች አሉ

ለሄሞዳያሊስስ ሶስት የተለያዩ የመዳረሻ ዓይነቶች ሊቀመጡ ይችላሉ። AV-ፊስቱላሰው ሠራሽ የደም ሥሮች እና ካቴተር ይባላሉ። የሚከታተልዎት ሐኪምዎ ስለ እያንዳንዳቸው ጥቅሞች እና ጉዳቶች ሊያስተምርዎት ይገባል።

1.   AV-ፊስቱላ

  • ለሄሞዳያሊስስ AV-ፊስቱላ ምርጥ ምርጫ ነው። ብዙ ሰዎች የዚህ አይነት መዳረሻ ያገኛሉ። ምክንያቱም AV-ፌስቱላ ብዙውን ጊዜ ለብዙ ዓመታት የሚቆይ ነው በተጨማሪ ደም የመርጋት ወይም የኢንፌክሽን የመጋለጥ እድላቸው ዝቅተኛ ነው። በዚህ ሂደት የደም ወሳጅ ስርን ከደም መላሽ ስር ጋር በቀዶ ሕክምና በማገናኘት የሚደረግ የመዳረሻ አይነት ነው።
  • AV-ፊስቱላ ለዳያሊስስ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ከ2 እስከ 4 ወራት ወይም ከዚያ በላይ መቆየት አለበት። ስለዚህ ዳያሊስስን ከመጀመርዎ በፊት AV-ፊስቱላ ከወራት በፊት መደረግ አለበት። ይህም የዳያሊስስ ህክምና በሚፈልጉበት ጊዜ ለመዘጋጀት በቂ ጊዜ ይፈቅዳል።
  • AV-ፊስቱላን ለመፍጠር አነስተኛ ቀዶ ጥገና ያስፈልጋል። ብዙውን ጊዜ ለፊስቱላዎ ተመራጭ ቦታ ክንድ ነው።

AV-ፊስቱላ ጥቅሞች:

  • ረዘም ላለ ጊዜ ይቆያል
  • ለበሽታ/ወይም ኢንፌክሽን የማይጋለጥ ነው
  • ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ እጅግ በጣም ጥሩ የደም ፍሰትን ይሰጣል
  • ለደም መርጋት የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው

2. ሰው ሠራሽ የደም ሥሮች/AV-graft

  • ይህ ምርጫ የደም ስር ቀዶ ጥገና ሐኪም ሰው ሠራሽ የደም ሥሮች/ ቱቦ ይጠቀማል። ይህ የደም መላሽ እና ደም ወሳጅ ሥሮችን በልዩ ሰው ሠራሽ ቱቦ በመቀላቀል በቀዶ ሕክምና የሚደረግ የዲያሊሲስ ዓይነት ነው።
  • AV graft ብዙውን ጊዜ በክንድዎ መታጠፊያ ውስጥ ወይም በላይኛው ክንድ ውስጥ ይደረጋል። አንዳንድ ጊዜ በእግርዎ ወይም በደረትዎ ግድግዳ ላይ ሊቀመጥ ይችላል። የ AV graft በአጠቃላይ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ቢያንስ ለሁለት ሳምንታት መቆየት ያስፈልገዋል።
  • ምንም እንኳን ይህ ምርጫ ደም የመርጋት ዕድሉ ከፍ ያለ ቢሆንም ትንንሽ ደም መላሽ ሥሮች ካሉዎት የተሻለው አማራጭ ሊሆን ይችላል።

3. ማዕከላዊ የደም ሥር ካቴተር/ Central Catheter

  • ይህ የተደራሽነት ምርጫ ብዙውን ጊዜ በአንገት ላይ ይቀመጣል። ካቴቴሮች ለስላሳ የፕላስቲክ ቱቦዎች የተሰሩ ናቸው። ካቴተር አብዛኛውን ጊዜ ለጊዜያዊ መዳረሻ ጥቅም ላይ ይውላል።
  • አብዛኛውን ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለው አፋጣኝ ዳያሊስስ አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ወይም ሰዎች ሌላ መዳረሻ ከሌላቸው ነው።
  • ካቴቴሮች ከፊስቱላ ወይም ከግራፍቶች ይልቅ ብዙ ችግሮች (እንደ መርጋት እና ኢንፌክሽኖች) አለባቸው። ለጥሩ ዳያሊስስ ሕክምና በቂ የደም ፍሰት ላይኖራቸው ይችላል።

ቀጠሮ ለመያዝ ወይም ስለ ዳያሊስስ ተደራሽነት ጥያቄዎች ካሉዎት፣ የሄሞዳያሊስ ተደራሽነት አማራጮችዎን ለመረዳት፣ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለማድረግ እና ለራስዎ ወይም ለምትወዷቸው ሰዎች የሚቻለውን እንክብካቤ ለማረጋገጥ ዛሬ ይደውሉ።

ለሁሉም አይነት ዳያሊስስ ተደራሽነት የደም ስር ቀዶ ጥገና ሐኪም ቀጣይነት ያለው የጥገና አገልግሎት ይሰጣል፣ ይህም የደም መርጋትን እና ኢንፌክሽኖችን ለመከላከል ይረዳል።